| 08.01.2009 | 14:00 UTC
የእሥራኤል ፍልሥጤም ተኩስ-አቁም ንግግር
በእሥራኤልና በሐማስ መካከል ተኩስ-አቁም ለማስፈን የተያዘው የዲፕሎማሲ ጥረት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። የፍልሥጤም ራስ-ገዝ አስተዳደር፣ የእሥራኤልና ጋዛን የሚቆጣጠረው የሐማስ ንቅናቄ ተጠሪዎች ዛሬ ካይሮ ላይ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል። ሆኖም ፍልሥጤማውያን ቡድኖች ከወዲሁ የግብጽ የተኩስ-አቁም ዕቅድ ተቀባይነት አይኖረውም እያሉ ነው። እሥራኤል በበኩሏ ተኩስ-አቁሙን ለመቀበል ከጋዛ አኳያ የሚካሄደው የሮኬት ተኩስ መቆሙን፤ እንዲሁም ከግብጽ ወደ ጋዛ የጦር መሣሪያ ማሾለኩ ማብቃቱን ቅድመ-ግዴታ አድርጋለች። እሥረኤል ከትናንት ጀምሮ የአየር ድብደባዋን በቀን ለሶሥት ሰዓት ጊዜ ጋብ ማድረጓ አይዘነጋም። ይሁንና ለዲፕሎማሲ ጥረት ወደ ቴላቪቭ የተጓዙት የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ፖሊሲ ተጠሪ ሃቪየር ሶላና ዕርምጃውን ባይከፋም በቂ ሆኖ አላገኙትም። ዘላቂ ተኩስ-አቁም ይበልጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት በጋዛ ውዝግብ ላይ የጋራ ውሣኔ ለማስተላለፍ ተስኖት እንደቀጠለ ነው። ም/ቤቱ ከሶሥት ቀናት ክርክር በኋላም አንድ አቁዋም ሊይዝ አልቻለም። ምዕራባውያኑ መንግሥታት አሜሪካ፣ ብሪታኒያና ፈረንሣይ ካይሮና ፓሪስ በጊዜ ለተገደበ ተኩስ-አቁም የጀመሩትን የሰላም ጥረት የሚደግፍ የውሣኔ ረቂቅ ሲያቀርቡ የአረብ መንግሥታት በአንጻሩ ዘላቂና በዓለምአቀፉ ሕግ መሠረት አሣሪ የሆነ ውሣኔ መተላለፍ አለበት ባይ ናቸው። ይህ በዚህ እንዳለ የጋዛ ድብደባ ከተጀመረ ወዲህ ከሊባኖስ አኳያ በእሥራኤል ሰሜናዊት ከተማ ናሃሪያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሮኬቶች ተተኩሰዋል። ፖሊሲ እንዳስታወቀው በጥቃቱ ሳቢያ በርካታ ሰዎች መለስተኛ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሩሢያና ኡክራኒያ በጋዝ ውዝግባቸው መነጋገር ጀመሩ
በጋዝ ዋጋ የተነሣ ብርቱ ውዝግብ ላይ ወድቀው የሰነበቱት ሩሢያና ኡክራኒያ ችግሩን ለመፍታት እንደገና እየሞከሩ ነው። የሩሢያው መንግሥታዊ ኩባንያ የጋዝፕሮም ሃላፊ አሌክሤይ ሚለርና የኡክራኒያው ናፍቶጋዝ አቻቸው ኦሌግ ዱቢና ሞስኮ ላይ ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ሁለቱ የቀድሞ ሶቪየት ሬፑብሊኮች አውሮፓን ፈተና ላይ ለጣለው የጋዝ አቅርቦት መተጓጎል እርስበርሳቸው ሲወናጀሉ ሰንብተዋል። የሩሢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቭላዲሚር ፑቲን በበኩላቸው ጉዳዩ በዓለምአቀፍ ታዛቢዎች እንዲጣራ የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል በስልክ ያቀረቡላቸውን ሃሣብ ደግፈዋል። የሩሢያና የኡክራኒያ ተጠሪዎች በአውሮፓ ሕብረት አስተናጋጅነት ለመደራደር ዛሬ ማምሻውን ብራስልስ ይገባሉ። የአውሮፓ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ የሕብረቱ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት የሁለቱ አገሮች የዋጋ ጭቅጭቅ እስረኛ መሆኑ አግባብ የለሽ እንደሆነ አስገንዝበዋል። የአውሮፓ ሕብረት አገሮች ከሚፈጁት ጋዝ ሩቡን የሚያስገቡት ከሩሢያ ነው።
በኦጋዴን የታገቱ የዕርዳታ ሠራተኞች ነጻ ተለቀቁ
በኢትዮጵያ የኦጋዴን ምሥራቃዊ አካባቢ በሶማሌ ታጣቂዎች ታግተው የቆዩ ሁለት የዕርዳታ ሠራተኞች ነጻ ተለቀቁ። ጃፓናዊቱ ሃኪም ካይኮ አካሃኔና የኔዘርላንዱ ተወላጅ የዕርዳታ ሠራተኛ ቪለም ሱልስ ነጻ መውጣታቸውን በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረጉት የጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሜዲሢን-ዱ-ሞንድ የተሰኘው የፈረንሣይ የሕክምና በጎ አድራጎት ድርጅት ናቸው። ሁለቱ ሰዎች ከሶማሊያ በሚዋሰነው የኦጋዴን አካባቢ ተጠልፈው የተወሰዱት ባለፈው መሥከረም ወር ነበር። ሜዲሢን-ዱ-ሞንድ በጉዳዩ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ሁለቱ ሰዎች ትናንት ከተለቀቁ በኋላ አስተማማኝ ወደሆነ ቦታ ተወስደዋል። ታጋቾቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሲጠቀስ በሌላ በኩል ለአጋቾቹ ካሣ ይከፈል-አይከፈል የታወቀ ነገር የለም። አጋቾቹ ቀደም ሲል ሶሥት ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈላቸው ጠይቀው ነበር።
ፓኪስታን በቦምቤይ ጥቃት የዜጋዋን ተሳትፎ አመነች
የፓኪስታን መንግሥት የአገሪቱ እሥላም አክራሪዎች በቅርቡ በሕንድ ታላቅ ከተማ በቦምቤይ ተካሂዶ በነበረው ጥቃት መሳተፋቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ አመነ። የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት እንዳረጋገጠው ከአጥቂዎቹ መካከል በሕይወት የተረፈውና በሕንድ የተያዘው ብቸኛው ግለሰብ አጅማል-አሚር-ካሣብ የፓኪስታን ዜጋ ነው። እሥላምአባድ ይህን እስካሁን ስትቃወም ቆይታለች። የፓኪስታን መንግሥት የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪውን ሜሕሙድ-አሊ-ዱራኒን ጠቃሚ በሆኑ የደህንነት ጥያቄዎች ላይ የመንግሥትን ውሣኔ አላከበሩም ሲልም ከሥራ አሰናብቷል። ባለፈው ሕዳር ወር ቦምቤይ ውስጥ ደርሶ በነበረው የአክራሪዎች ጥቃት ከ 170 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸው አይዘነጋም። ከነዚሁ መካከል ዘጠኙም ሽብርተኞች ነበሩ።
የኮንጎ ተኩስ-አቁም ንግግርና የዓማጺያኑ ክፍፍል
በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ መንግሥትና ዓማጺያን መካከል ተኩስ-አቁም ለማስፈን ባለፈው ሰኞ እንደገና የጀመረው የናይሮቢ ንግግር በዓማጺያኑ ክፍፍል ሳቢያ ይበልጥ ውስብስብ እየሆነ ነው። ክፍፍሉ ይበልጥ ጎልቶ የወጣው በሣምንቱ መጀመሪያ እንኩንዳ በአመራር ጉድለት መወገዳቸውን በማመልከት ተቀናቃኛቸው ቦስኮ ናጋንዳ መግለጫ ካወጡ በኋላ ነበር። ናጋንዳ በዛሬው ዕለት እንኩንዳ ከሥልጣን መወገዳቸውን ተቀብለው ከአዲሱ ብሄራዊ የሕዝብ መከላከያ ሸንጎ ከ CNDP አመራር ጋር እንዲተባበሩ መጋበዛቸውን አንድ የቡድኑ ቃል-አቀባይ ለአሶሺየትድ ፕሬስ ዜና አገልግሎት አስረድቷል። ቃል አቀባዩ ጨምሮ እንዳስገነዘበው ናይሮቢ የሚገኙት ዓማጺያንም ድርጅቱን አይወክሉም። ሎራን እንኩንዳ በበኩላቸው በድርጅቱ ውስጥ አንዳች ክፍፍል እንደሌለ ቀደም ሲል ገልጸው ነበር። ሎራን እንኩንዳ ከሶሥት ዓመታት በፊት በመሠረቱት የዓመጽ ቡድን በምሥራቃዊው ኮንጎ የጥቃት ዘመቻ ሲያካሂዱ ባለፈው ነሕሴ ወር ተባብሶ በቀጠለው ውጊያ ሩብ ሚሊዮን ሕዝብ መፈናቀሉ ይታወቃል።
ፑንትላንድ አዲስ ፕሬዚደንት ሰየመች
የሶማሊያ ተሰንጣሪ ግዛት ፑንትላንድ አዲስ ፕሬዚደንት ሰየመች። የአጋቾችና የባሕር ወንበዴዎች መነሻ በመሆን የታወቀችው ግዛት ም/ቤት ፕሬዚደንቱን የመረጠው በዛሬው ዕለት ነው። አሶሺየትድ ፕሬስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው አዲሱ መሪ አብዲራሕማን-ፋሮሌ የባሕር ውንብድናን እታገላለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል። በሌላ በኩል የፑንትላንድ መማክርት በገንዘብ በመገዛት የባሕር ወንበዴዎቹን ይደግፋሉ በመባል ይወቀሳሉ። በሌላ ዜና ደግሞ በሶማሊያ ጠረፍና በሕንድ ውቂያኖስ ላይ ውንብድናውን ለመታገል ዓለምአቀፍ ሕብረት መፈጠሩን አሜሪካ አስታውቃለች። የሕብረቱ ተግባር በያዝነው ጥር አጋማሽ የሚጀምር ሲሆን በአንድ የአሜሪካ የጦር መኮንን የሚመራ መሆኑም ተያይዞ ተጠቅሷል።




