| 11.03.2010 | 15:00 UTC
ጀርመን፤ የትምሕርት ቤት ግድያ ታሰበ
በጀርመን ባደን-ቩርተንበርግ ክፍለ-ሐገር መንደር በቪነንደን አልበርትቪል ትምሕርት ቤት ውስጥ አሰቃቂ ግድያ የተካሄደበት አንደኛ ዓመት ዛሬ ታስቦ ዋለ። 900 ገደማ የሚጠጉ ተማሪዎች፣ መምሕራንና የሰለቦቹ ቀሪ ቤተሰብ ዓባላት ከትምሕርት ቤቱ ፊትለፊት በሚገኝ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ዕለቱን በሃዘን አስታውሰዋል። ከአንድ ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት አንድ የ 17 ዓመት ወጣት ተማሪ ተኩስ ከፍቶ ዘጠኝ መሰሎቹንና ሶሥት መምሕራንን መግደሉ ይታወሣል። ወጣቱ በሽሽት ላይ እንዳለ ተጨማሪ ሶሥት ሰዎችን ገድሎ የራሱን ሕይወት ማሳለፉም አይዘነጋም። የትምሕርት ቤቱ አስተዳዳሪ አስትሪድ ሃን እንዳስረዱት ግድያው ያስከተለው የመንፈስ ስቃይ ዛሬም ለብዙ መምሕራን ፈታኝ እንደሆነ ነው። የቪነንደን አብያተ-ክርስቲያን ዛሬ ጧት ላይ ደወል በመደወል ተኩሱ የተከፈተበትን ሰዓት ሲያስቡ ይህንኑ ተከትሎም የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለር በተገኙበት ይፋ የሃዘን ስነ-ስርዓት ተካሂዷል። ኮህለር በስነ-ስርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር የአገሪቱ የመሣሪያ ባለቤትነት ሕግ እንዲጠብቅ ጥሪ አድርገዋል።










