| 03.12.2008 | 14:00 UTC
ኦስሎ፡ የተስፈንጣሪ ቦምቦች ምርት አጋጅ ውል ፍረማ በኖርዌይ
ከአንድ መቶ ሰባት የዓለም ሀገሮች የተውጣጡ ተወካዮች በዓለም ተስፈንጣሪ ቦምቦች የሚታገዱበትን ውል ለመፈራረም ዛሬ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ ይገናኛሉ። ውሉ የተስፈንጣሪ ቦምቦችን ምርት፡ ዝውውር እና ክምችትን ያግዳል። ከአይሮፕላኖች የሚወረወሩት ወይም ከመድፎች የሚተኮሱት ተስፈንጣሪ ቦምቦች በአየር ላይ እንዳሉ ከፈነዱ በኋላ በመቶ የሚቆጠሩ ንዑሳን ቦምቦች በሰፊ አካባቢዎች ላይ ይበተናሉ። ግን ብዙዎቹ ሲቭሉ ህዝብ የሚኖርባቸውን ሰፊ አካባቢዎች ላይ ካረፉ በኋላ ስለማይፈነዱ በሚነካኩበት ጊዜ በህዝብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ተገልጾዋል። ዓለም አቀፍ የአካል ተጎጂዎች ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሰረት፡ እአአ ከ1965 ዓም ወዲህ በዓለም በተጣሉት ተስፈንጣሪ ቦምቦች ወደ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ አንድም ተገድሎዋል ወይም የአካል ተጎጂ ሆኖዋል። ከነዚህም መካከል ዘጠና ስምንት ከመቶው ሲቭል ህዝብ ነው። የውሉ ፍረማ ትልቅ አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን የአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አባል የሆኑት ጀርመናዊው ኡሊ አንከን ገልጸዋል። « አንድ የጦር መሳሪያ ዓይነት በጠቅላላ በሚያስከትለው አስከፊ ሰብዓዊ ጉዳት ሰበብ ከብዙ የዓለም አቀፍ ማህበረ ሰብ ጥረት በኋላ አሁን የታገደበት አሰራር ትልቅ እመርታ ነው። »በዓለም ትልቆቹ የተስፈንጣሪ ቦምብ አምራቾችና ተጠቃሚዎች የሆኑት ዩኤስ አሜሪካ፡ ሩስያ፡ ቻይና፡ እስራኤል፡ ህንድና ፓኪስታን ተስፈንጣሪ ቦምቦችን ምርት ዕገዳን በመቃወም ውሉን እንደማይፈርሙ አስታውቀዋል።




